settings icon
share icon
ጥያቄ፤

የሕይወት ትርጉም ምንድ ነው?

መልስ፤


የሕይወት ትርጉም ምንድ ነው? በሕይወቴ ውስጥ ምን ባደርግ ነው ዓላማ፣ ስኬትና እርካታ የማገኘው። ዘላቂ ውጤት ያለው ሥራ ለማከናወን አቅሙ ይኖረኝ ይሆን? ብዙ ሰዎች ስለዚህ ጉዳይ ጥያቄ ማንሳታቸው አይቀርም። በሕይወታቸው ለማሳካት ያሰቡትን ጉዳይ ቢፈፅሙም ከአመታት በኋላ መለስ ብለው ከሰዎች ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንዴት እንደተበላሸና ባዶነት ለምን እንደሚሰማቸው ሳይገርማቸው አይቀርም። አንድ የቤዝ ቦል ተጫዋች በዘርፉ ከፍተኛ ዝና ከተቀዳጀ በኋላ ጨዋታ ሲጀምር ሰዎች ምን ብለው ቢነግሩት ይመርጥ እንደነበር ቢጠይቁት “ከፍተኛ ደረጃ ከተደረሰ በኋላ ምንም እንደሌለ ቢነግሩኝ እመርጥ ነበር” ሲል በቁጭት ተናግሯል።

ብዙ ግቦች ባዶነታቸው የሚረጋገጠው እነሱን ለማከናወን በርካታ ዓመታት ካለፈ በኋላ ነው። በኛ ሰብዓዊ ሕብረተሰብ ትርጉም እናገኛለን ብለው በማሰብ ብዙ ሰዎች በርካታ ዓላማዎችን ያራምዳሉ። ከነዚህም የሕይወት ዓላማዎች የንግድ ስኬት፣ ሐብት፣ መልካም ግንኙነት፣ ወሲብ፣ መዝናናትና ለሌሎች ሰዎች ጥሩ ነገር መስራትን ያካትታሉ። ሰዎች ሲመሰክሩ እንደተስተዋለው ሐብት የማከማቸት፣ መልካም ግንኙነት የመመስረትና ደስታን የማግኘት ዓላማቸውን ቢያሳኩም ማንም ሊሞላው የማይችል ባዶነት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።

የመፅሐፈ መክብብ ፀሐፊ ይህንን ስሜት ለመግለፅ “ከንቱ!...የከንቱ ከንቱ! ሁሉ ከንቱ ነው” ይላል(መፅሐፈ መክብብ 1፡2)። የመፅሐፈ መክብብ ፀሐፊ የሆነው ንጉሥ ሰለሞን ከልክ በላይ የሆነ ሐብት፣ በእርሱ ዘመንና በኛ ጊዜ ከነበረ ማንም ሰው የሚበልጥ ጥበብ፣ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ዕቁባቶች፣ መንግስታት የሚቀኑበት ቤተመንግስትና የአትክልት ስፍራ፣ ምርጥ የሆነ ምግብ፣ ወይንጠጅና አለየተባለ መደሰቻና መዝናኛ ነበረው። ጠቢቡ አንድ ጊዜ ሲናገር ልቡ የተመኘውን ያሳድድ ነበር። በዓይኖቻችን የምናየውና በስሜቶቻችን የምናጣጥመው ኑሮ ብለን የምንኖረው “ከፀሐይ በታች ያለው ሕይወት” ከንቱ ነው ሲል አጣጥሎታል።

ይህ ባዶነት ለምን ተከሰተ? ምክንያቱም እግዚሐብሔር የፈጠረን የዚህና አሁን ከምንለማመደው ባሻገር ላለው ነገር ነው። ሠለሞን ስለእግዚሐብሔር ሲናገር “ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው” ብሏል። (መፅሐፈ መክብብ 3፡11)። ሁላችንም በልባችን እንደምናውቀው ያለው ነገር “እዚህና አሁን” ያለው ብቻ እንዳልሆነ እንገነዘባለን። የመፅሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ መፅሐፍ በሆነው በዘፍጥረት ውስጥ እግዚሐብሔር የሰው ልጅን በራሱ መልክ እንደሰራው እናነባለን። (ዘፍጥረት 1፡26)። እኛ ከሌላ ነገር (ከሌላ የሕይወት ቅርፅ) ይልቅ አፈጣጠራችን ወደ እግዚሐብሔር የቀረበ እንደሆነ የሚያሳየን ነው። ከዚህም በተጨማሪ የምናገኘው ነገር የሰው ልጅ በኃጢት ወድቆ የኃጢያት መርገም በምድር ላይ ከመምጣቱ በፊት የሚከተሉት ነገሮች ተግባራዊ ሆነዋል። (1) እግዚሐብሔር ሰውን ማህበራዊ ፍጡር አድርጎ አበጀው።(ዘፍጥረት 2፡ 18-25)፣ (2) እግዚሐብሔር ለሰው ልጅ ሥራ ሰጠው። (ዘፍጥረት 2፡ 15)፣ (3)እግዚሐብሔር ከሰው ጋር ህብረት ነበረው። (ዘፍጥረት 3፡ 8) እና (4) ሰው ምድርን እንዲገዛ እግዚሐብሔር ሥልጣን ሰጠው። (ዘፍጥረት 1፡ 26)። የእነዚህ ነገሮች ትርጉም ምንድ ነው? እነዚህ እያንዳንዱ ለሕይወታችን እርካታ እንዲያስገኙልን ነው። እግዚሐብሔር አቅዶ የነበረው፣ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ (በተለይም ሰው ከእግዚሐብሔር ጋር ያለው ህብረት) ተለዋውጠዋል። ምክንያቱም የሰው ልጅ በኃጢያት ከወደቀ በኋላ እርግማን በምድር ላይ ተግባራዊ በመሆኑ ነው። (ዘፍጥረት 3)።

የመፅሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ ክፍል በሆነው በራዕይ መፅሐፍ እግዚሐብሔር አንድ ነገር አስቀምጧል። አሁን በተጨማጭ የምናውቃቸውን ምድርና ሰማይን አስወግዶ አዲስ ምድርና ሰማይን በመፍጠር ዘላለማዊ ሕይወትን ይተካል። በዚያን ጊዜ ከዳነው የሰው ልጅ ጋር ሙሉ ህብረት ያደርጋል። ያልዳኑትን ይፈርድባቸውና እርባናየለሽ ተብለው ወደ እሳትባህር ይጣላሉ። (ራዕይ 20፡ 11-15)። የኃጢያት መርገም ይወገዳል። ከዚህ በኋላ ኃጢያት፣ ሐዘን፣ በሽታ፣ ሞትና ስቃይ ከቶ አይኖርም።( ራዕይ 21፡ 4)። አማኞችም ሁሉን ነገር ይወርሳሉ፣ እግዚሐብሔር ከእነርሱ ጋር ይኖራል፣ እነሱም ልጆች ይሆኑታል። (ራዕይ 21፡ 7) ።

ስለዚህ ወደ ሙሉ ክብ መጣን ማለት ነው። እግዚሐብሔር ከእርሱ ጋር ህብረት እንድናደርግ ፈጠረን። የሰው ልጅ ኃጢያት በመስራቱ ህብረቱ እንዲቋረጥ አደረገ። እግዚሐብሔር ከመረጣቸው ጋር ህብረቱን እንደገና በማደስ በላይኛው ቤት ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ ያደርጋል። በሕይወት ዑደት ውስጥ ብዙ ነገር ካሳኩ በኋላ ለዘላለሙ ከእግዚሐብሔር ጋር መለያየት ከውድቀት ሁሉ የከፋው ነው። ነገር ግን እግዚሐብሔር ዘላለማዊ ደስታ ዕውን የሚሆንበትን መንገድ ከመቀየሱም ባሻገር(ሉቃስ 23፡ 43) በምድርም ላይ ሕይወት አርኪና ትርጉም ያለው እንዲሆን ሁኔታዎችን አመቻችቶአል። እንዴት ነው ይህ ዘላለማዊ ደስታና “ገነት በምድር” የሚገኘው?

በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የታደሰው የሕይወት ትርጉም

አሁን በምድርና በሚቀጥለው ሕይወት በሰማይ የሕይወት እውነተኛ ትርጉም የሚገኘው ከእግዚሐብሔር ጋር ተቋርጦ የነበረው ግንኙነት እንደገና ሲታደስ ነው። ይህ ግንኙነት አዳምና ሔዋን በኃጢያት በመውደቃቸው ምክንያት ተቋርጦ ነበር። ዛሬ ያ ግንኙነት እውን የሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (የሐዋሪያት ሥራ 4፡ 12፣ ዮሐንስ 14፡ 6፣ ዮሐንስ 1፡ 12)። የዘላለም ሕይወት የሚገኘው እርሱ/እርሷ ኃጢያታቸውን ተናዘው ሲፀፀቱ (በኃጢያታቸው ሥራ ላለመቀጠልና ክርስቶስ ለውጦ አዲሰ ሰው እንዲያደርጋቸው ሲፈልጉ ነው) እና ኢየሱስ ክርስቶስ እንደአዳኛቸው ተቀብለው ሲደገፉበት ነው። (በዚህ ጠቃሚ ጉዳይ የበለጠ ማብራሪያ ለማግኘት “የድነት ዕቅድ ምንድ ነው?” የሚለውን ጥያቄ ተመልከት)።

በሕይወት እውነተኛ ትርጉም የሚገኘው ኢየሱስን እንደየግል አዳኝ ብቻ በመቀበል አይደለም (ይህ በራሱ ድንቅ ቢሆንም) ይልቁንም የሕይወት እውነተኛ ትርጉም የሚገኘው አንድ ሰው እንደ ደቀመዝሙር ሲከተለውና ከእርሱ በመማር ቃሉ ከሆነው መፅሐፍ ቅዱስ ጋር ጊዜ ሲያሳልፍና በተጨማሪም በፀሎት ሕብረት ሲኖረውና ትዕዛዙን በማክበር እርምጃውን ከርሱ ጋር ሲያደርግ ነው። ምናልባት አንተ ያላመንክ ብትሆን (ወይም ምናልባት አዲስ አማኝ ከሆንክ) “በጣም የሚያጓጓ ወይም ለኔ ነገሩ አርኪ አይደለም” ልትል ትችላለህ። ነገር ግን እባክህን ንባብህን ለጥቂት ጊዜ ቀጥል። ኢየሱስ የሚከተሉትን ሐሳቦች ሰንዝሯል። “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፣ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፣ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” (ማቴዎስ 11፡ 28-30)። “እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ” (ዮሐንስ 10፡ 10)። “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፣ ስለእኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል።(ማቴዎስ 16፡ 24- 25)። በእግዚሐብሔር ደስ ይበልህ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።(መዝሙር 37፡ 4)።

እነዚህ ሁሉ ጥቅሶች የሚያብራሩት ምርጫ እንዳለን ነው። የራሳችንን ኑሮ ልንመራ እንችላለን፣ ውጤቱ ግን ባዶ ሕይወት ነው። ወይም በሙሉ ልብ እግዚሐብሔርን በመከተል ለሕይወታችን ያለውን ዓላማ በመሻት እርካታና ስኬት ማግኘት ነው። ይህም የሚሆነው ፈጣሪያችን ስለሚወደንና መልካም የሆነውን ሁሉ ለእኛ ስለሚመኝልን ነው።(ቀላል ሕይወት ላይሆን ይችላል፤ ግን አርኪ ነው።)

የፕሮፌሽናል ጨዋታ ተመልካች ብትሆንና ለመከታተል ወደ እስታዲየም ብትሄድ ጥቂት ዶላሮችን ከመክፈልክ ራቅ ያለ መቀመጫ ይሰጥሃል። በርካታ ዶላሮች ከከፈልክ ግን ጨዋታውን ቀረብ ብለህ እንድታይ ጥሩ እይታ ያለው መቀመጫ ታገኛለህ። በክርስትና ሕይወትም እንዲሁ ነው። እግዚሐብሔር ተዓምር ሲሠራ ማየት ከተፈለገ እሁድ ብቻ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች አይሆንም። ዋጋውን አልከፈሉማ። እግዚሐብሔር ተዓምር ሲሰራ የሚያዩት ከልባቸው የክርስቶስ ደቀመዝሙር በመሆን የራሳቸውን ሃሳብ ማሳደድ ትተው የእግዚሐብሔርን ዓላማ የሚያራምዱ ናቸው። ዋጋ ከፍለዋል(ለክርስቶስና ለፍቃዱ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ሰጥተዋል)። ሕይወትን በደንብ ከማጣጣማቸውም በላይ ያለአንዳች ፀፀት በፈጣሪያቸው ፊት ሊቀርቡ ይችላሉ። በራሳቸው አያፍሩም። በሌላ ሰው ፊት ሲቀርቡም አይሸማቀቁም። አንተስ ይህንን ለመፈፀም ፈቃደኛ ነህን? እንዲህ ከሆነ ሕይወቴ ትርጉምና ዓላማ የለውም የሚል ቁጭት አያድርብህም።

English



ወደ አማርኛ መነሻ ገጽ ለመመለስ

የሕይወት ትርጉም ምንድ ነው?
© Copyright Got Questions Ministries