settings icon
share icon
ጥያቄ፤

ጽድቅ ምንድነው?

መልስ፤


በቀላሉ ለማስቀመጥ፣ መጽደቅ ማለት፣ ጻድቅነትን ማወጅ ማለት ነው። ጽድቅ ማለት የእግዚአብሔር ሥራ ሲሆን፣ እሱም ኃጢአተኛውን ጻድቅ አድርጎ የሚያውጅ ነው፣ ያ ኃጢአተኛ በክርስቶስ ካለው እምነት የተነሣ። ጽድቅ ላይ ዋነኛው ሐሳብ፣ የጻድቁ ፈራጅ የእግዚአብሔር አዋጅ ነው፣ ይኽውም በክርስቶስ የሚያምን ሰው፣ ምንም ያህል ኃጢአተኛ ቢሆንም፣ ጻድቅ ነው - እንደ ጻድቅ ይታያል፣ ምክንያቱም ከክርስቶስ የተነሣ ከእግዚአብሔር ጋር ወደ ጽድቅ ግንኙነት ስለሚመጣ።

በሚገባ ለመረዳት፣ ጽድቅ የሚሆነው እግዚአብሔር ስለ ኃጢአተኛው የሚያውጀው ነው፣ በኃጢአተኛው ውስጥ ከሚሆን አንዳችም ለውጥ ሳይሆን። ያም ማለት፣ ከውስጥ ባለ ባሕርይ የሆነ ጽድቅ ማንንም ቅዱስ ሊያደርገው አይችልም፤ እሱ እንዲያው የሚያውጀው፣ በእግዚአብሔር ፊት በደለኛ እንዳልሆነ፣ እና ስለዚህ እንደ ቅዱስ መወሰዱን ነው። ኃጢአተኛው ወደ ቅድስና የሚለወጥበት ሁኔታ የሚፈጠረው በቅድስና ነው፣ እሱም ከጽድቅ ጋር የሚያያዝ፣ ነገር ግን ለፍቺ ሲባል፣ ከእሱ ይለያል።

ከአማኞች ጋር በተያያዘ ጽድቅን የሚገልጸው ቁልፍ ምንባብ ሮሜ 3፡21-26 ነው፡ “አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥ እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ። እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ … ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው።” በርከት ያሉ ጠቃሚ ሐቆች፣ ስለ ጽድቅ ተመዝግበዋል፡
• ጽድቅ የሚመጣው ከሕግ በተለየ ነው፤ ማለትም፣ ጽድቅን ሕግን በመጠበቅ ወይም በገዛ ራሳችን መልካም ሥራ ልናገኘው አንችልም።
• ጽድቅ ሊሆን የሚችለው በክርስቶስ መሥዋዕታዊ ሞት ነው፤ እሱም የተመሠረተው በፈሰሰው በክርስቶስ ደም ነው።
• ጽድቅ ነጻና ልግስናዊ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፣ የኢየሱስ ክርስቶስን መሥዋዕትነት በእምነት ለተቀበሉት የተሰጠ።
• ጽድቅ የእግዚአብሔርን ጻድቅነት ያሳያል።

እግዚአብሔር ኃጢአተኛን ከማጽደቁ ጋር በተያያዘ በርካታ ነገሮች አሉ፡
1) የኃጢአት ቅጣት ዋጋ፣ እሱም ሞት መሆኑ (ሮሜ 3፡23፤ 8፡1፤ 1 ጴጥሮስ 2፡24)።
2) ወደ እግዚአብሔር ሞገስ መመለስ፣ እሱም በኃጢአታችን ምክንያት ያጣነው (ዮሐንስ 3፡36)። ስለዚህ፣ ጽድቅ ጥፋተኛ ካለመሆን ፍርድ ይበልጣል፤ እሱ ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት ማግኘት ነው። እኛ አሁን የእግዚአብሔር ወዳጆች ነን (ያዕቆብ 2፡23) እናም ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን (ሮሜ 8፡17)።
3/ በጽድቅ ላይ የሚነሣ ክስ/ነቀፋ፣ እሱም የክርስቶስ ጽድቅ የሚያቃልለው፣ የእኛን ያለፈ ታሪክ (ሮሜ 4፡5-8)። እኛ ጻድቅ እንሆን ዘንድ ታውጇል፣ ከሙግት (ሕግ) አኳያ ምክንያቱም “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው” (2 ቆሮንቶስ 5፡21)።

ጸድቀናል፣ ጻድቅ መሆናችንም ታውጇል፣ በደኅንነታችን ቅጽበት። ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሥራውን አጠናቋል፣ ለእኛ መጽደቅ የሚያስፈልገውን። “ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን!” (ሮሜ 5፡9)። እንግዲያውስ እሱ “እኛን ስለ ማጽደቅም የተነሣ” ነው። (ሮሜ 4፡25)።

የሚነሣው ጥያቄ፣ “ጽድቅ ልክ ነውን? እሱ ቅዱስ ከሆነ፣ እግዚአብሔር እንዴት በደለኛውን ኃጢአተኛ ይቅር ሊል ይችላል?” መልሱ፣ ጽድቅ ለኃጢአታችን ሰበብ አያቀርብም፣ ኃጢአታችንን ችላ አይልም፣ ወይም ኃጢአታችንን አይደግፍም። ይልቁንም ኃጢአታችን ሙሉ ለሙሉ ተቀጥቷል፣ ክርስቶስ ለእኛ ብሎ ኃጢአታችንን ወስዷል። እሱ የእኛ ምትክ ነው (1 ጴጥሮስ 3፡18)። የእግዚአብሔር ቁጣ በክርስቶስ ከመፈጸሙ የተነሣ (ኢሳይያስ 53:4–6)፣ ከኵነኔ ነጻ ሆነናል (ሮሜ 8፡1)፣ እናም እግዚአብሔር ሁለቱንም ሆኖ ይቀራል፣ “ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው” (ሮሜ 3፡26)።

እግዚአብሔር እኛን በጸጋው፣ በክርስቶስ ባለን እምነት ስላጸደቀን፣ እኛ አሁን ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም አለን (ሮሜ 5፡1)። ልክ እንደ ካህኑ ኢያሱ፣ “እድፋሙን ልብሳችንን” አውልቀን (ዘካርያስ 3፡4)፣ በምሳሌ እንዳለው እንደ አባካኙ ልጅ፣ አሁን እኛ “ምርጡን ካባ” ለብሰናል (ሉቃስ 15፡22)። እግዚአብሔር አብ እኛን የሚመለከተን እንደ ፍጹምና ነውር የሌለብን አድርጎ ነው፣ እኛም “መልካም የሆነውን ለማድረግ” መሰጠት ይኖርብናል (ቲቶ 3፡14)።

ሮሜ 5፡18-19 በተብራራው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ፣ የጽድቅን መሠረትና ውጤት ያጠቃልለዋል፡ “በዚህን ምክያት፣ በአንዱ መተላለፍ የተነሣ [የአዳም ኃጢአት] በሰዎች ሁሉ ላይ ኵነኔ ደረሰ፣ ከአንዱም የጽድቅ ሥራ የተነሣ ለሰዎች ሁሉ የሕይወት ጽድቅ ሆነ። በአንድ ሰው አለመታዘዝ ምክንያት [ለማድመጥ አለመቻሉ፣ ግዴለሽነቱ] ብዙዎችን ኃጢአተኛ እንዳደረገ፣ በአንድ ሰው መታዘዝ ምክንያት፣ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ፣ በእግዚአብሔር ፊትም ተቀባይነት ያገኛሉ፣ በእርሱ ፊትም በጽድቅ ይቆማሉ።”

Englishወደ አማርኛ መነሻ ገጽ ለመመለስ

ጽድቅ ምንድነው?
© Copyright Got Questions Ministries